እንኳን ለብርሃነ ትንስኤ በሰላም በጤና አደረሳቹ
‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ... :፡›› መዝ.፸፯፥፷፭
በዲ/ን ሄኖክ ኃይሌ
‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ
የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ ፤ የዘላለም ኀሣር ሰጣቸው፡፡›› መዝ.፸፯፥፷፭
የወይን ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው፤ ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ ፤ የዘላለም ኀሣር ሰጣቸው፡፡›› መዝ.፸፯፥፷፭
እስራኤላውያን አምላካቸው እግዚአብሔር ፈርኦንን ከነሠራዊቱ በባሕረ ኤርትራ አስጥሞ ከባርነት ነጻ ካወጣቸው በኋላ ፣ በምድረ በዳ እንደበጎች እየመራ ርስቱን በገመድ ካካፈላቸው በኋላ ያደረገውን ረስተው አሳዘኑት፡፡ ‹‹አስቆጡት ምስክሩንም አልጠበቁም ፤ እንደ አባቶቻቸውም ከዱ ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ ፣ በኮረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቆጡት ፣ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት፡፡
እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቆጣ እስራኤልን እጅግ ናቀ ፤ የሴሎምን ማደሪያ ተዋት›› /መዝ. ፸፯፥፶፯/ በሕዝቡም ላይ ተቆጥቶ በጠላት እጅ እንዲወድቁ አደረገ፡፡ በዚህ ቁጣ የተነሣ ርስቱን ቸል አላቸው ፣ ጎልማሶቻቸውን እሳት በላቸው ካህናቶቻቸው በሰይፍ ሲወድቁ ያለቀሰ የለም፡፡ ለቅሶ በሁሉም ቤት ነበርና አጽናኝ ለመሆን የሚችል ማንም አልነበረም፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ለፍጥረቱ የሚራራ አምላክ በምርኮ የወደቁትን ሕዝቡን አሰበ፡፡ ‹‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ ፤ የወይንም ስካር እንደተወው እንደ ኃያልም ሰው ፤ ጠላቶቹንም በኋላው መታ ፤ የዘላለም ኀሣር ሰጣቸው፡፡››
መድኃኔዓለም ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው!
ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ እግዚአብሔር ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የሚለው ስም በተናጠልም በአንድነትም ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይነገራል፡፡ ሐዋርያዊው ቅዱስ አትናቴዎስ ‹‹አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ›› ‹‹እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ ስለ ወልድ ስለ መንፈስ ቅዱስ እላለሁ›› ብሏል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ‹‹ቃልም እግዚአብሔር ነበረ›› ፤ ‹‹አምላክ በእልልታ እግዚአብሔር በመለከት ድምጽ ዐረገ›› በሚሉትና በሌሎችም ጥቅሶች ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን…›› የሚለው የመጽሐፍ ቃል ሲተረጎም ‹‹እግዚአብሔርነቱ / እግዚአብሔር መሆኑ ፣ መለኮትነቱ ከሙታን እንዳስነሣው›› ተብሎ ነው፡፡ (ሮሜ ፲፥፱) ስለዚህ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመጥራት እግዚአብሔር ብሎ መጥራት በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ የተለመደና የታወቀ ነገር ነው፡፡ ‹እግዚአብሔር ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ› በሚለውም ኃይለ ቃል ላይ ወልደ አብ ወልደ ማርያም ክርስቶስ ‹‹እግዚአብሔር» ተብሎ ተጠርቷል፡፡
ትንሣኤ ከእንቅልፍ እንደ መነሣት
በዚህ የቅዱስ ዳዊት ትንቢት የጌታችን ሞት በእንቅልፍ የተመሰለ ሲሆን ትንሣኤው ደግሞ ከእንቅልፍ በመንቃት ተመስሎአል፡፡ በእርግጥም ሞት በመጽሐፍ ቅዱስ በእንቅልፍ ይመሰላል፡፡ ራሱ ጌታችን አልዓዛር በሞተ ጊዜ ‹‹ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል ከእንቅልፉ ላስነሣው እሔዳለሁ አላቸው፡፡ እንግዲህ ደቀመዛሙርቱ ፡- ጌታ ሆይ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት፡፡ ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር ፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደተናገረ መሰላቸው፡፡ እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ አልዓዛር ሞተ… አላቸው፡፡›› ዮሐ. ፲፩፥፲፫ ቅዱስ ጳውሎስም ስለሞቱ ሰዎች ለመናገር ሲል ‹‹አንቀላፍተው ስላሉቱ…›› ብሏል:: በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታዎች አንድን ሰው ሞተ ከማለት ይልቅ ‹‹አንቀላፋ›› የሚለው አገላለጽ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ አነጋገር ሲሞቱ አንቀላፉ ተብሎ የተጻፈላቸው ነገሥታትና መሳፍንት በብሉይ ኪዳን ከሠላሳ በላይ ናቸው፡፡ በሐዲስ ኪዳንም ቅዱስ ሉቃስ የሊቀ ዲያቆናት እስጢፋኖስን ሞት ሲዘግብ ‹‹ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ። ይህንም ብሎ አንቀላፋ።›› ሲል ገልጾታል፡፡ (ሐዋ. ፯፥፷)
እንቅልፍ ከሰው ልጅ ቁጥጥር ውጪ የሆነ ሒደት ነው፡፡ ሰው መተኛትም አለመተኛትም በእርሱ ቁጥጥር አይደለም፡፡ መተኛት ፈልገው እንቅልፍ አጥተው የሚሰቃዩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ እንቅልፍ በዝቶባቸው በፈለጉት ጊዜ ለመነሣት የሚቸገሩም አሉ፡፡ የሚያስተኛም የሚያነቃም እግዚአብሔር ነው፡፡ ለሚሻው እስከ ስድሳ ስድስት ዓመታት እንቅልፍ ሲሰጥ አይተናል በተቃራኒው እንቅልፍ በአይናቸው እንዳይዞር ያደረጋቸውም አሉ፡፡ ‹‹እኔ ተኛሁ አንቀላፋሁም እግዚአብሔርም ደግፎኛልና ነቃሁ››እንዲል፡፡መዝ. ፫፥፭ እንዲሁም ሞት በእግዚአብሔር ሥልጣን ያለ ነው፡፡ ሰው ተኝቶ ሳይነሣ እንደማይቀር በእንቅልፍ የተመሰለው ሞትም ትንሣኤ ያለበት ነው፡፡ ተኝተን እንደማንቀር ሞተንም አንቀርም፡፡
የጌታችን ሞት ደግሞ ከሰው ልጆች ሁሉ ሞት በላይ እንደሰመመን እንቅልፍ የሚቆጠር ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን በሥጋ ቢሞትም በመለኮቱ ግን ንቁህ ነው፡፡ ‹‹እኔ ተኝቻለሁ ልቤ ግን ነቅቷል›› እንዲል መጽሐፍ (መኃ.፭፥፪) ጌታችን በሥጋው ሲሞት በመለኮቱ ግን ሕያው ነበር፡፡ ለዚህም ነው በዕለተ አርብ በበዓለ ስቅለት ‹‹ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ›› ‹‹በስጋ ሞትን የቀመስከው ሆይ!›› እያልን የምንሰግደው፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስም ‹‹በሥጋ ሞተ በመንፈስ ግን ሕያው ሆነ›› ሲል ተናግሯል፡፡ (፩ጴጥ. ፫፥፲፰)
የጌታችን ሞቱ በእንቅልፍ እንደሚመሰል በምሥጢር የሚያስረዳን ምሳሌም ከኦሪትም እንጥቀስ፡፡ እግዚአብሔር በአዳም ላይ እንቅልፍን ጣለበት በዚህ ሰዓት አዳም ማዕከለ ነቂህ ወነዊም /በመንቃትና በመተኛት መሃል ነበር/ ፤ በዚህ እንቅልፍ ላይ ሳለ ከጎኑ ሔዋንን ፈጠረ ፤ ሔዋን ማለት የሕያዋን ሁሉ እናት ማለት ነው፡፡ ጌታችንም በዕለተ አርብ በመስቀል ላይ በሥጋ ሞቶ በመለኮቱ ግን ሕያው ሆኖ እያለ ጎኑን ሲወጋ ከጎኑ በፈሰሰው ደምና ውኃ የሕያዋን ሁሉ እናት የሆነች ጥምቀት ተገኝታለች፡፡ ጌታችን ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ የሚለውም ኃይለ ቃል በሥጋው ከሞተው ሞት በሥልጣኑ አፈፍ ብሎ እንደተነሣ በምሳሌ የሚያስረዳ ነው፡፡
ትንሣኤ ስካር እንደመተው
ሌላው በቅዱስ ዳዊት ቃለ ትንቢት የሚገኘው ሃሳብ ትንሣኤ የወይን ስካር እንደመተው ተመስሎአል፡፡ ስለዚህ ሁለተኛው ሞትን እንደስካር የመመሰሉ ቁም ነገር ነው፡፡ በእርግጥ ስካር ለጌታችን የሚነገር ነገር አይደለም፡፡
ስካርን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ‹‹የፈቃድ ዕብደት›› ብሎ ይጠራዋል፡፡ ስካር ታላቁን ጻድቅ ኖኅን እንኳን ያዋረደ ነበር፡፡ ይህ ጻድቅ ሰው ያለ ልማዱ ጥቂት ወይን ቢጠጣ ከአናቱ ላይ ወጥቶ ራሱን አስጣለው፡፡ ዕርቃኑንም ሆነ ፤ ለደፋር ልጁ ለካም መሳቂያና መሳለቂያም ሆነ፡፡ ይሁንና ታማኝ ልጆቹ ሴምና ያፌት የአባታችንን ዕርቃን አናይም ብለው ሸፈኑት፡፡ (ዘፍ. ፱፥፳፩) ታዲያ እንዲህ ዕርቃን የሚያስጥለው ስካር እንዴት ለእግዚአብሔር ይነገራል፡፡ ‹‹የወይን ስካር እንደተወው›› ማለትስ ምን ማለት ነው?
በእርግጥም በጌታችን ሕይወት ስካር ታይቷል ፤ ነገር ግን ስካሩ በመጠጥ ሳይሆን በፍቅረ እጓለ እመሕያው (በሰው ልጆች ፍቅር ነው)፡፡ ኖህ ሰክሮ ዕርቃኑን እንደሆነ ጌታችን በሰው ልጆች ፍቅር ሰክሮ ዕርቃኑን ተሰቅሏል፡፡ በኖህ ላይ ልጁ ካም እንዳፌዘበት አይሁድ በጌታችን ላይ ዘብተዋል፡፡ ሴምና ያፌት የአባታችንን ዕርቃን አናይም ብለው ዐይናቸውን ጨፍነው የኋሊት እየሔዱ በነጠላ እንደሸፈኑት ጌታችን ዕርቃኑን በተሰቀለበት ዕለት ፀሐይ የጨለመችው ጨረቃ ደም የመሰለችው ፣ ከዋክብትም የረገፉት ብርሃንን ያለበሳቸውን አምላክ ዕርቃኑን ላለማየት ነበር ‹‹ከመ ኢይርአዩ ዕርቃኖ ለዘአልበሶሙ ብርሃነ፤ ብርሃን ያለበሳቸውን ዕርቃኑን ሆኖ እንዳያዩ›› እንዲል፡፡
ጠላቶቹንም በኋላው ገደለ ፤ የዘላለም ኀሣር ሰጣቸው፡፡
ጌታችን ጠላቶቹን በኋላው መታ ሲባል ከኋላው በተተከለ በመስቀሉ ጠላቶቹ የሆኑት አጋንንትን ድል መንሳቱን የሚያስረዳ ነው፡፡ ስለ ዲያቢሎስ ሲናገርም መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡- ‹‹እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።›› (ቆላ. ፪፥፲፬) ለዘላለምም ለሠራዊተ አጋንንት በመስቀሉ መሰቃየትን ፣ መስቀሉን ሲያዩ መደንገጥና መሳቀቅን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህንን ያደረገ ልዑለ ባሕርይ እግዚአብሔር ስሙ ይክበር ይመስገን!
መልካም የትንሣኤ በዓል!!
የብጹዕ አባታችን ቃለ ምዕዳን